የጳጉሜ ቀናት በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለፀ።
።።።።።።።።።።።።።።።።
ፐብሊክ ሰርቪስ፤ ነሐሴ 29/2016 ዓ.ም
የመንግሥት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት 5ቱን የጳጉሜ ቀናት አከባበር አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል።
መግለጫዉን የሰጡት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ከበደ ዴሲሳ ለአዲሱ ዘመን መሻገሪያ የሆኑት እነዚህ ቀናት በለዉጡ ዓመታት የተገኙ ስኬቶችን ለማክበር እንዲሁም ድክመቶችን ለማረም እድል የሚሰጡ ናቸው ብለዋል።
ባለፉት ዓመታት አገርን ሊያፈርሱ የሚችሉ ግጭቶችና የዉጪ ጣልቃ ገብነቶችን በመቋቋም የተጋረጡብንን ፈተናዎች መመከት ችለናልም ነው ያሉት።
በዚህም የመጀመሪያው የጳጉሜ ዕለት በ“መሻገር ቀን” በሁሉም መልክ መሻገራችንን የምናሳይበት ዕለት ይሆናልም ብለዋል።
የህዳሴ ግድብ ሀይል ማመንጨት፣የአምራች ኢንዱስትሪዎች መነቃቃት፣የስንዴ ምርታማነት መጨመር መሻገራችንን ማሳያ ስኬቶች ስለመሆናቸውም ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተዋል።
“የሪፎርም ቀን” ተብሎ በተሰየመዉ ጳጉሜ 2 የኢትዮጵያ ተቋማትን በተሻለ መልኩ በማዘመን የህዝቡን ፍላጎት ማሟላት ላይ እንደሚያተኩርም ነው የተጠቀሰው።
ጳጉሜ 3 “የሉዓላዊነት ቀን” ተብሎ የተሰየመ ሲሆን በዕለቱ አገሪቱ የገጠሙዋትን ሉዓላዊነትን የሚገዳደሩ ፈተናዎችን የተቋቋመችበት አንድነት ይዘከራል።
በዕለቱ ከቀኑ 6 ሰዓት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ሁሉም ሰዉ ባለበት ሆኖ የኢትዮጵያ ብሄራዊ መዝሙር እንደሚዘመርም ተነግሯል።
ጳጉሜ 4 “የህብር ቀን” ሲሆን በዕለቱ “ህብራችን ለሰላማችን” በሚል መሪ ቃል የአብሮነት እሴትን በሚያጎለብቱና ህብረብሄራዊ አንድነትን በሚያፀኑ ዝግጅቶች ይከበራል።
በጳጉሜ 5 “የነገ ቀን” ተብሎ የተሰየመ ሲሆን ዕለቱ ነገን ታሳቢ ያደረጉ የአገር ግንባታ ስኬቶችና በአገር ግንባታ ሂደት ውስጥ የወጣቱን ሚና በሚያስገነዝቡ ሁነቶች ይከበራል።
5ቱ የጳጉሜ ቀናት በሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች፣በፌዴራል የመንግስት ተቋማት፣በዉጪ አገራት በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንፅላ ፅ/ቤቶች እንዲሁም በመላው ማህበረሰብ ዘንድ እንደሚከበር የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት በመግለጫው አመላክቷል።